ከዚህ በታች የሰፈሩትን አስር የመጠይቅ ነጥቦች ለራሳችሁ ፍጹም እውነተኛ በመሆንና መልስን በመስጠት ምን ያህል አንድን ስህተት የምትደጋግሙ መሆናችሁን ለማየት ሞከሩ፡፡
1. ባለህበት እንደምትረግጥ ይሰማሃል?
2. አንድ እንቅፋት ሲያጋጥምህ ለመፍትሄ የሚሆኑ አዳዲስ መንገዶችን የመሞከር መነሳሳቱ የለህም?
3 ደጋግመህ እዚያው ችግር ላይ ራስህን ስለምታገኘው፣ አጉል ባህሪዎችንና ልማዶችን ለማቆም ያቅትሃል?
4 ግብህን ለመምታት ለምን እንዳልቻልክ ጊዜ ወስደህ ለማሰብና መፍትሄ ለማግኘት ብቃቱና መነሳሳቱ እንደሌለህ ይሰማሃል?
5. አጉል ልማዶችህን ለመቀየር ባለመቻልህ በራስህ ላይ የማዘንና የመበሳጨት ዝንባሌ አለህ?
6. ሁለተኛ አልደግመውም ያልከውን ስህተት ደግመህ ደጋግመህ ስታደርገው ራስህን ታገኘዋለህ?
7. አዳዲስ የመሻሻል መንገዶችን በመሞከር “ከመድከም ይልቅ ባሉበት መቀጠል ቀላል እንደሆነ ታስባለህ?
8. ባለህ ዲሲፕሊን የማጣት ሁኔታ ምክንያት ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ያጠቃሃል?
9. ነገሮች በጠበካቸው መልኩ ካላገኘሃቸው ጨክኖ ከመቀጠል ይልቅ የጀመርከውን ራስን የመለወጥ ጉዞ ለማቋረጥ እንደምክንያት ትጠቀምበታለህ?
10. ስለምትደጋግማቸው ስህተቶች የቅርብ ወዳጆችህ ሲጠቁመህ የመከላከልና የመቆጣት ዝንባሌ ይታይብሃል?
ከላይ ለተጠየቁት አስር ጥያቄዎች ከግማሸ በላይ ለሆኑት “አዎ” የሚል መልስ ከሰጠህ ስህተትን የመደጋገም ዝንባሌ ሊኖርህ ስለሚችል ለጕዳዩ ትኩረት በመስጠት ለውጥን ለማስተናገድ ጥረት አድርግ፡፡
ስህተትን ልምምድ ከመደጋገም ይልቅ ራስን በማሸነፍ ከስህተት የመማር ከሚሰጠን በርካታ ጥቅሞች መካከል ሶስቱን ላጋራችሁ፡፡
1. የማያቋርጥ መሻሻል
ቀና በልና ዙሪያህን ተመልከት፡፡ አሁን አንተ የደረስክበትን ደረጃ አይተህ ሊደረስበት ከሚቻለው ሌላ ደረጃ ጋር ስታነጻጽረው መሻሻልን ላትፈልገው አትችልም፡፡ መሻሻል ደግሞ የሚመጣው ያለፈውን ስህተት ላለመድግም በመወሰንና፣ ይልቁንም ካለፈው ስህተት በመማር ነው::
2. -ጤናማ ድፍረት
ጤናማው ድፍረት ያለንበትን ቦታ ስናውቅና አምነን ስንቀበል፣ በመቀጠልም የት መሄድ እንዳለብን ተገንዝበን አስፈላጊውን እርማት ስንወስድ የሚመጣ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ካለማቋረጥ ስንሻሻል የምንሸማቀቅበት ነገር ስለማይኖረን ግልጽ ከመሆን የሚመጣ ድፍረት ማዳበር እንጀምራለን፡፡
3. ለሌሎች አስተማሪ የመሆን እድል
አንዳንድ ጊዜ በንባብና በመሳሰሉት ሁኔታዎች ከሰዎች ቅድመ-ልምምድ ያገኘናቸው ትምህርቶች ሙሉ ትርጉም እኛው ራሳችን በዚያ ሁኔታ እስክናልፍ ድረስ አይገባንም፡፡ ይህ ማለት፣ ወድቀን የተነሳንባቸውና ተሳስተን የታረምንባቸው ሁኔታዎች ከራሳችን አልፈን ሌሎችን እስከመምከር የምንደርስበት እውነተኛ አስተማሪያችን ነው፡፡